የካቲት 2015 ዓ.ም
በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚደንት ውስጥ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ክትትል ሁሉን አቀፍ ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸው የፈጠራ ስራዎች በመምህራን እና ተማሪዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ የፈጠራ ስራዎቹ እውቅና አግኝተው ዘርፉ የሚፈልገውን ስታንዳርድ አሟልተው ወደ ገበያ መቅረብ እንዲችሉ በአዕምራዊ ንብረት ባለቤትነት የተመዘገቡ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን የሰሯቸው ስድስት የፈጠራ ስራዎች የባለቤትነት መብት የሚያረጋግጥ የአዕምሯዊ ንብረት እና የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡
የፈጠራ ስራዎቹ በሶፍትዌር ዘርፍ ላይ ችግር ፈች የሆኑ የዕለት ተዕለት ስራዎችን የሚያቀላጥፉ እና የሚያቃልሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ አቶ በረከት ዋለ የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ይህን አስመልክተው ሲገልፁ ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት የአዕምሯዊ ንብረት እና የቅጅ እና ተዛማጅ መብቶች ምዝገባ ለማድረግ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም የአዕምራዊ ንብረት እና የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን በሚመለከት ስልጠናዎችን አዘጋጅቶ ለፈጠራ ባለቤቶች መስጠቱን ገልፀዋል፡፡ ይህም መምህራን እና ተማሪዎች የፈጠራ ስራዎቻቸውን በአዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት አስመዝግበው የባለቤትነት መብታቸውን እንዲያረጋግጡ ግንዛቤ መፍጠሩን አስታውሰዋል፡፡ በዚህም መሰረት የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ስድስት የሶፍትዌር የፈጠራ ስራዎችን ለአዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት በመላክ እንዲመዘገቡ በማድረግ የእውቅና ሰርቴፍኬት ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ያገኙት ግለሰቦች፡
1. ነብያት በቀለ በ Advance searching API
2. መርዕድ ንጉሴ በ Research and Knowledge Sharing Platform
3. ኤርሚያስ በቀለ Enkopazion
4. ናትናዔል ሻውል Brain Storm Engineering 2D Design Draft
5. ዮናስ ተስፋየ- Financial Archive and Payment Auto Mailing
6. ዮናስ ተስፋየ- በ Human Resource Management System ናቸው፡፡
እነዚህ የፈጠራ ስራዎች በዩኒቨርሲቲው መምህራን እና ተማሪዎች የተሰሩ ሲሆን መረጃ በደንቡ ለመመዝገብ እና ለመያዝ ፤ለመማር ማስተማር አገልግሎት እና የምርምር ስራዎችን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ መሆናቸውን አቶ በረከት ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የፈጠራ ስራዎች ከዩኒቨርሲቲው አልፈው ወደ ገበያ በሚገቡበት ወቅት ለመሰል ተቋማት ችግር ፈች እና የተቀላጠፈ አሰራርን በመዘርጋት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡ የፈጠራ ስራ የአንድ ጊዜ ክስተት አለመሆኑን እና ይልቁን የተራዘመ ሂደትን የሚጠይቅ እንደመሆኑ የፈጠራ ባለቤቶች ይህንን ሂደት አልፈው ለዚህ በመብቃታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ በረከት ሌሎች የፈጠራ ስራዎች በአዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት እንዲመዘገቡ መላካቸውን እና ዩኒቨርሲቲው ከምንጊዜውም የበለጠ ፈጣሪዎችንና የፈጠራ ስራን ለማበረታታት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡