የአአሳቴዩ አዲስ ገቢ ተማሪዎች የስልጠናና የውይይት መድረክ ተጀመረ

የአአሳቴዩ በ2010 ዓ.ም. ልዩ የመግቢያ ፈተና በመስጠት ለተቀበላቸው ተማሪዎች ለሁለት ቀናት የሚቆይ የስልጠናና የውይይት መድረክ ጀመረ፡፡

የአአሳቴዩ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኑርልኝ ተፈራን ጨምሮ ሌሎች የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራር አካላት ከተማሪዎች ጋር ትውውቅ ያደረጉ ሲሆን  ፕሬዘዳንቱ በመሩት በመጀመሪያው ቀን ውይይት የውጤታማ  ትግበራ ልኬት (Deliverology)አሰራር ስርዓት እንዲሁም የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ክፍተቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች በሚሉ ርዕሶች ዙርያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱም በመጀመሪያ ድግሪ ከሚመረቁ ተማሪዎች ውስጥ 90% የሚሆኑት በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ስራ መቀጠር/መፍጠር የሚችሉ እንዲሆኑ ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝ በመድረኩ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት  የdeliverology Unity አስተባባሪ ዶ/ር ኤፍሬም ግደይ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ጉዳይ ቁልፍ ተግባር በመሆኑ ዩኒቨርስቲው በመምህራን ቅጥር፤ ቤተሙከራ(laboratory)  ግንባታና ሌሎች አካዳሚያዊ ጉዳዮችን ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሌላው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ጉዳይ የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን የተመለከተ ሲሆን በቀደሙት ዘመናት የነበሩ መልካም ሥነ-ምግባሮች እየጠፉና እየተሸረሸሩ መሔዳቸው በግልጽ የሚታይ መሆኑንን ያወሱት የመወያያ ጽሁፍ አቅራቢው አቶ ብሩክ፣ ፕሮግራሙ የአገሪቱ ተረካቢ የሆኑ ወጣቶችን  መልካም ባህሪ የሚያላብስ ይሆን ዘንድ ስርዓተ ትምህርቱ ላይ የሚታዪ ችግሮችን ከማስተካከል አንጻር በሰፊው ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በመድረኩ የተነሱ ጉዳዮችን መሰረት አድርገው ተማሪዎች ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን  ያነሱ ሲሆን በጽሁፍ አቅራቢዎች ተገቢው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ተማሪዎች ወደፊት ሊከተሉዋቸው የሚገቡ የሥነ-ምግባር ደንቦችንና በአጠቃላይ የዩኒቨርስቲው አሰራር ዙርያ በሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ማብራሪያ የሚቀርብላቸው ሲሆን የ2010ዓ.ም ዕቅድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Related posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *