የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኑርልኝ ተፈራ በ27ኛው ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓል ላይ ያደረጉት ንግግር

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኑርልኝ ተፈራ በ27ኛው ዓመት  የግንቦት 20 የድል በዓል ላይ ያደረጉት ንግግር

ግንቦት 17፣2010 ዓ.ም

 

የተከበራችሁ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አመራር አባላት

የተከበራችሁ መምህራንና ሰራተኞች

የተከበራቸሁ ተማሪዎች

 

ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለ27ኛው ዓመት የግንቦት 20 የድል በዓል አደረሳችሁ በማለት የተሰማኝን ደስታ በራሴና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

 

ይህ በአገራችን ለ27ኛ ጊዜ በዩኒቨርሲቲያችን ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ የሚከበረው የግንቦት 20 የድል በዓል “የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ለላቀ አገራዊ ስኬት” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፣ ዕለቱም ያለፉትን የስኬት ዓመታት በመዘከር እና ውስንነቶችን በማረም፣ ለወደፊት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ ፣ጠንክረን እንደምንሰራ ቃል የምንገባበት እለት ነው፡፡

 

ክቡራትና ክቡራን

 

የላቀ ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ለላቀ አገራዊ ስኬት” ስንል የሚከተሉትን መልዕክቶችን በውስጡ ይዞ ይገኛል፡፡

 

በፍቅር የተሳሰረ የህዝባችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለህዳሴያችን መተኪያ የሌለው መሆኑን፣ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለአገራችን ዘላቂ ሠላምና እድገት ዋስትና ስለመሆኑ ፣ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የህልውናችን መሠረቶች እና  ግንቦት ሀያ ለደረስንበት ደረጃ ፅኑ መሰረት መጣሉን እንዲም የአገራችንን ዘላቂ ሰላም ጠብቀን ለማስቀጠል ፣በትግል ሂደት ያጋጠሙንን ፈተናዎች በማለፍ ዕድገታችንን እነድናስቀጥል እና መጪው ዘመን ብሩህ እንድናደርግ መሪ ቃሉ ያስገነዝባል፡፡

 

ክቡራትና ክቡራን

 

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ እንዲመጣ የሚጠበቀውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ከማፋጠን አንጻር እንዲሁም ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎረሜሽን አገራዊ እቅድ ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ፣ ኢንዱስትሪው አሁንና ለወደፊት የሚፈልገውን የሰው ሃይል ለማፍራት፣ የዛሬውን ችግር ለመፍታትም ሆነ ለወደፊት የሚያስፈልጉንን ቴክኖሎጅዎች ላይ በማተኮር ምርምሮችን በመስራትና የአካባቢውን ማህበረሰብ ሊጠቅሙ የሚችሉ አገልግሎቶችን በመስጠት ድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

 

በዚህ ረገድ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ የምናስመርቃቸውን ተማሪዎች ጨምሮ፣ ስራ የጀመሩትን የልህቀት ማዕከላት ፣ በመቋቋም  ላይ የሚገኙ ማዕከላዊ የምርምር ላብራቶሪዎች፣እንዲሁም በአዲስ መልክ የጀመርናቸው በርካታ የ2ኛ እና የ3ኛ ድግሪ ፕሮግራሞች መልካም ምሳሌ ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

 

የዩኒቨርሲቲያችንን ራዕይና ግብ ማዕከል ባደረገ መልኩ ከአለም ዓቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና ድርጅቶች ጋር በጋራ በመስራት ላይ የምንገኝ ሲሆን ፣በዚህ ዘርፍም ምርምሮችን እና የስርዓተ-ትምህርት ቀረፃዎችን (Curriculm designing ) በጋራ በመስራት ላይ  እንገኛለን፡፡የሚመሰረቱት ግንኙነቶችና ስምምነቶችም ከልህቀት ማዕከላቱ ጋር የተገናኙ እንዲሆኑም ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

 

ክቡራትንና ክቡራን

 

በአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ሀገራችን ለበርካታ ጊዚያት  የተጓዘችበት የማሽቆልቆል ሂደት ተገቶ፣ በእድገትና ዴሞክራሲ አቅጣጫ የተጓዘችባቸው ዓመታት ነበሩ፡፡ በማንኛውም መስፈርት ሲመዘን መሰረታዊ የአቅጣጫ ለውጥ ተግባራዊ በተደረገባቸው በእነዚህ ዓመታት፣ እልህ አስጨራሽ ትግል ተካሂዷል፡፡

ለዚህ ስኬት እንድንበቃ ላደረጉን ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ምስጋና ይግባና፣ አዲሱ ትውልድ አገሪቱ ለዘመናት ከተተበተበችበት የድህነት አዙሪት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ ከተረባበረበና ይህንን ታሪክ መስራት ከቻለ፣ የቀደመው ትውልድ የከፈለውን መስዋእትነት በከንቱ ላለመቅረቱ ዋስትና ይሆናል፡፡ እዚህ በመካከላችን የምትገኙ ተማሪዎችና ወጣቶችም ይህንን አገራዊ ራዕይ እውን እንደምታደርጉ ሙሉ እምነቴ ነው፡፡

 

ክቡራትና ክቡራን

መተኪያ የሌላት ውድ እናት ሀገራችንን ወደ እድገት ጎዳና ለመምራት ፣ ሁላችን በፍቅር ፣ በአንድነት፤  ከሁሉም በላይ ደግሞ በቅንነት ልንሰራላት ይገባል እላለሁ፡፡ ይህ የሚጀምረው ደግሞ እያንዳዳችን በተሰማራንበት የስራ መስክ የተሰጠንን ሥራ በአግባቡ ፣በታማኝነትና በቅንነት  ሰርተን ስንገኝ ነዉ፡፡ ስለዚህም በየተመደባችሁበት የሥራ ዘርፍ  ፣የየበኩላችሁን ከተወጣችሁ፣ ዩኒቨርሲቲያችንን ብሎም አገራችንን ታላቅ እናደርጋለን ብዬ አምናለሁ ፡፡

 

በመጨረሻም በዓሉ የተሳካ እንዲሆን እየተመኘሁ፣ በድጋሚ  እንኳን  ለግንቦት 20 የድል በዓል  በሰላም  አደረሳችሁ እላለሁ፡፡

 

አመሰግናለሁ !    

 

መልካም የድል በዓል ይሁንልን!

 

ዶ/ር ኑርልኝ ተፈራ

ግንቦት 17፣2010 ዓ.ም

 

Related posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *