የዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ የህይወት ታሪክ በአጭሩ

ቀን ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም

የዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ የህይወት ታሪክ በአጭሩ

ዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ ከአባታቸው ከአቶ አሰፋ መኩሪያ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ አታለለች በላይ ንጋቱ ግንቦት 24 ቀን 1958 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ቦታው አራት ኪሎ በሚባለው ሰፈር ተወለዱ፡፡  እድሜያቸውም ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤት ተምረዋል፡፡

ከዚህም በመቀጠል ወደ ባህር ማዶ ተጉዘው የመጀመሪያ ፣ የሁለተኛ  እና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሶቭየት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ አገር በኢኮኖሚክስ          የትምህርት መስክ ስቴስቲክስን ዋና የሥልጠና መስክ አድርገው ከ1976 ዓ.ም እስከ 19981 ዓ.ም ሁሉንም ዲግሪዎች ከሞስኮ ኢንስቲትዩት  ኦፍ ኢኮኖሚክስ ኤንድ ስታስቲክስ አጠናቀው ተመርቀዋል፡፡ በቋንቋ ክህሎታቸውም እንግሊዝኛን፣ አማርኛን፣ ራሽያኛን አልፎ አልፎም ፈረንሳይኛን ይጽፉና ይናገሩ ነበር፡፡

ዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ ለቤተሰቦቻቸው ሁለተኛ ልጅ ሲሆኑ በ1980 ዓ.ም  ከአቶ ፈንታሁን እርካታ ጋር ትዳር የመሰረቱ ሲሆን፣ ባለቤታቸው በ1981 ዓ.ም ቀደም ብሎ በሞት የተለያቸው ቢሆንም ከትዳራቸው አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡

ዶ/ር አፀደም ከትዳራቸው የወለዷትን ልጅ ረድኤት ፋንታሁንን አስተምረው ለወግ ለማዕረግ  አብቅተው የልጅ ልጅ ለማየት በቅተዋል፡፡

ዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ አገራቸውን እና ሕዝባቸውን በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው በታማኝነት፣ በቅንነት እና በታታሪነት አገልግለዋል፡፡

በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል፡-

  • ከ1997 ዓ.ም – 2000 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮንትራት መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡
  • ከጥቅምት 1998 – ህዳር 2001 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ /በአሁኑ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ/ የማስተርስ ዲግሪ አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡
  • በአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ተጠባባቂ ቢሮ ኃላፊ በመሆን መርተዋል፡፡
  • ከ2001 ጀምሮ በአድማስ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡
  • ከህዳር 2001- ነሐሴ 2001 በአዳማ ዩኒቨርሲቲ(ባሁኑ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ) የቢዝነስ ፋክሊቲ ዲን ነበሩ፡፡
  • ከህዳር 2002- ሚያዝያ 2003 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባዔ ሆነው አገልግለዋል፡፡
  • ከሚያዝያ 2003 – መጋቢት 2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሥራ አመራር ኢንስትቲዩት የኮሌጅ ዲን ሆነው ሰርተዋል፡፡
  • ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የቢዝነስ አማካሪ በመሆን በአለም ባንክ ድርጅት ተቀጥረው አገልግለዋል፣
  • ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሰርተዋል፡፡
  • በመጨረሻም ከጥቅምት 27/2006 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ህለፈተ-ሕይወታቸው ድረስ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በመምህርነትና በኮሌጅ ዲንነት አገልግለዋል፡፡

 

ከመንግስት መስሪያ ቤቶች በተጨማሪም በሌሎች የተለያዩ የግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች – በኦርቢት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ፣ በኒው ጀኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ በኩዊንስ ኮሌጅ፣ በዜጋ ቢዝነስ ኮሌጅ እና በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ዶ/ር አፀደ በህወት በነበሩ ግዜ ለስራቸው ትኩረት የሚሰጡ  ቅን ፣ቆራጥ ፣እና ታታሪ አመራርና ለሰዎችም አዛኝና መካሪ ነበሩ፡፡

ዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ በተወለዱ በ 51 ዓመታቸው በድንገተኛ ህመም ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡  የቀብራቸው ሥነ-ስርዓት በደብረ ሊባኖስ ገዳም ጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 7:00 ወዳጅ ፣ዘመዶቻቸውና፣የስራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡

ለቤተሰቦቻቸው፣ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን እንመኛለን፡፡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአፀደ ነፍስ(በገነት) ያኑርልን!

የዩኒቨርስቲያችን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኑርልኝ ተፈራም ለስራ ጉዳይ ከሄዱበት ውጭ አገር ሆነው በዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በራሳቸውና በዩኒቨርሲቲው ስም በደብዳቤና በስልክ ገልጸዋል፡፡ ለዶ/ር አፀደ ቤተስቦችና ለስራ ባልደረቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

 

የአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባ ጽ/ቤት ተወካይ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ተወካይ

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ የነበሩትና የዶ/ር አፀደ አሰፋ መኩሪያ ምክትል የነበሩት መምህር መክብብ ገ/ማርያም

ጥልቅ ሀዘናቸውን በቀብሩ ቦታ ተገኝተው ገልፀዋል፡፡

Related posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *