አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዜያት የማህበረሰቡን ህይወት እና ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ከዚህ በፊት ከሰራቸው አበይት ስራዎች መካከል ለ6 አቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤት እድሳት ፤ለአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት እንዲሁም በኮሮና ወረርሽን ወቅት አስፈላጊ የሆኑ ምግብነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ግብዓቶችን ለክፍለ ከተማው ማህበረሰብ እንዲዳረሱ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የ90 ቀናት የልማት ፕሮጀክት ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ለክፍለ ከተማው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ስራዎች ሰርቶ በዛሬው እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ እና የክፍለ ከተማው ስራ አስፈፃሚዎች በተገኙበት ተመርቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በራሱ ወጪ አሰርቶ ለክፍለ ከተማው ያበረከታቸው ስራዎች ከዩኒቨርሲቲው የቱሉዲምቱ በር እስከ ኮዬ ፈጨ አደባባይ ያሉ የመንገድ አካፋይ እና የመንገድ አደባባይ ማስዋብ፤ ለክ/ከተማው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ የዳቦ እና የአትክልት መሸጫ ሱቅ ፤እንዲሁም በክፍለ ከተማው የሚገኝ አንድ ቤተ-መፅሃፍት ከነ አጥሩ ሙሉ እድሳት በእለቱ ተመረቁ ስራዎች ናቸው፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ወቅት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዚደንቱ ተዋካይ የተቋማዊ ልማት እና ቢዝነስ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተመስገን ወንድሙ ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰቡ የሰራቸውን ስራዎች ለእንግዶች አስጎብኝተዋል፡፡ ዶ/ር ተመስገን ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ ውስጥ እንደመገኘቱ እና የህብረተሰቡን እድገት እና ለውጥ በብርቱ የሚፈልግ እንደመሆኑ የሚሰጠውን የማህበረሰብ አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ ከመማር ማስተማር፤ የምርምር ስራዎችን ከመስራት በተጨማሪ የአንድን ማህበረሰብ ኑሮ ሊያሻሽሉ የሚችሉ የማህበረሰብ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት ከዩኒቨርሲቲው ተልዕኮዎች ውስጥ አንዱና ዋንኛው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው በጥናት ላይ የተደገፉ ማህበረሰብ ተኮር ስራዎች ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል፡፡