የመግቢያ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለፀ ::

ወደ ሁለቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተና  በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለፀ ፡፡በ2010 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መሰናዶ ትምህርታቸውን አጠናቀው በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ካስቀመጠው መቁረጫ ነጥብ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ወደ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እና  አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ፈተና በተሳካ ሁኔታ ወስደዋል፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፍ በሃገራችን የልዕቀት ማዕከል የሆኑት ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በየአመቱ ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በፈተና አወዳድሮ መቀበል አራት አመት ያስቆጠሩ ሲሆን” ዘንድሮም በተለያዩ ክልሎች 36 የፈተና ጣቢያዎችን በመመደብ ፈተናውን እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ የቅድመ-ምረቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት  ዶ/ር ምስራቅ ግርማ እንደገለፁት” ለሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በዘንድሮው አመት ከአራት ሺ አራት መቶ ዘጠና ዘጠኝ በላይ ተማሪዎች  በኦንላይን(online) የተመዘገቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ከነዚህም ውስጥ 3500 ገደማ የሚሆኑት ተማሪዎች ለኢንጅነሪንግ ትምህርት ዘርፎች የተመዘገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ  999 ገደማ ደግሞ በተግባራዊ  ሳይንስ/አፕላይድ ሳይንስ/ የትምህርት ዘርፎች የተመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘው ከሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር “በሰላሳ ስድስቱም የፈተና ጣቢያዎች በቂ የሰው ሃይል ና የፈተና ግብአቶች መቅረባቸውን የገለፁት ዳይሬክተሯ” የኢንተርኔት ኮኔክሽን ችግሮች ሲፈጠሩ በባለሙያ ድጋፍ በተቻለ መጠን እንዲፈቱ መደረጋቸውን አክለው ለቢሯችን ገልፀዋል ፡፡

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ″ በፈተናው ወቅት ያነጋገርናቸው ተፈታኝ ተማሪዎችም ፈተናውን ያለምንም ችግር መፈተናቸውን ገልፀውልናል፡፡ተማሪ አብረሃም ውጅራ ከፋላሚን መሰናዶ ትምህርት ቤት 458 ውጤት በማምጣት በኦንላይን ተመዝግቦ ፈተናውን የወሰደ ሲሆን “ፈተናውን ካለፈ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ መማር እንደሚፈልግ ገልፆልናል፡፡ከዚህ ጋር አያይዞ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ለሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፍ  ከፍተኛ ትኩረት  በመሰጠት የፈጠራ እና ግኝት ስራዎች እንዲያድጉ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ አድንቆ ለቢሯችን ገልጧል፡፡ትህትና ኤርሚያስ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭት ናት፡፡ ትህትና ከቅድስት ማሪያም መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት 473 በማምጣት የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ፈተናውን የወሰደች ሲሆን በፈተናው ወቅት የተለየ  ችግር እንዳላጋጠማት ገልፃለች ፡፡

በመጨረሻም ለ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን  ለአዲስና ነባር ተማሪዎች ቅበላ  የተለያዩ ዲፓርትመንቶችና ሬጅስትራር አስፈላጊ ዝግጅቶች እያደረጉ መሆኑን ዶ/ር ምስራቅ ግርማ ለሪፖርተራችን ገልፀዋል፡፡