አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ፣በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ 1236 የ2015 ዓ.ም ተማሪዎች በደማቅ ስነ-ስርዓት አስመረቀ
************************
በምረቃው መርሃ-ግብር ማስጀመሪያ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ለ9ኛ ጊዜ ባዘጋጀው የ2015 ዓ.ም የእጩ ተመራቂ ተማሪዎች የምረቃ በዓል ላይ ለመታደም የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በምርቃ መልዕክታቸው ዶ/ር ደረጀ ዩኒቨርሲቲው የፈፀማቸውን አበይት ተግባራት ዘርዝርዋል፡፡
እንደ ፕሬዚደንቱ ገለፃ የትምህርት ጥራትና አግባብነትን ማረጋገጥ ዋነኛው የትምህርት መስክ የትኩረት አቅጣጫ በመሆን በሃገራችን ብሎም በዩኒቨርሲቲያችን በአትኩሮት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ዩኒቨርሲቲው የሚጠቀምበትን ስርዓተ-ትምህርት / ካሪኩለም ጊዜውን የዋጀ እና ተግባር እና ውጤት ተኮር በማድረግ የኢንዱስትሪውን እና የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማሳደግ ተቀርጾ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር ደረጀ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች በፈጠራ ስራ/ኢኖቬሽን እና ስራ ፈጠራ ኢንተርፕረነርሽም ችግር ፈቺ እና በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ እና ምሉእ ዜጋ እንዲሆኑ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በመተግበር ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲያችን ሀገራችን ላስቀመጠችው የልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ የእድገት እቅድ እንዲያግዙ ልዩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ከተቋቋሙት ሁለት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ እንደሆነ ያስረዱት ፕሬዚደነቱ በሀገራችን የልማትና እድገት ጉዞ እንዲመጣ የሚጠበቀውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ከማፋጠን አንጻር፣ የተተለመውን አገራዊ እቅድ ለማሳካት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሃይል በማፍራት በኩል እስከ አሁን ከ12,500 በላይ ተመራቂዎችን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ፒኤችዲ ዲግሪ አስመርቆ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዛሬው እለትም በመደበኛና በተከታታይ ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በቅድመ ምረቃ 943 ምሩቃን ከዚህም ውስጥ 839 በመደበኛ መርሃ

ግብር እና 104 ተማሪዎችን በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብር፤ በድህረ ምረቃ የማስተርስ ፕሮግራም 282 ምሩቃን ከዚህም ውስጥ 214 በመደበኛ መርሃ ግብር እና 68 ተመራቂዎች በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር እንዲሁም 11 ምሩቃንን በሶስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) በድምሩ በዚህ ዓመት 1236 ምሩቃን በዛሬው እለት የሚመረቁ ይሆናል ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት ለሁሉም የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው የመውጫ ፈተና በመደበኛው መርሃ ግብር 907 እና ከተከታታይ ትመህርት 115 በድምሩ 1022 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን የተፈተኑ ሲሆን 87 % የመደበኛ መርሃ ግብር ተማሪዎች ፈተናውን ያለፉ ሰሆን አጠቃላይ የተከታታይ ትምህርትን ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው 82% የመውጫ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች አልፈዋል፡፡ ይህም ውጤት እንደተቋም ከያዝነው 100% የማሳለፍ እቅድ ያነሰ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሰጠቱ እና ከነበረው አጠቃላይ የስነልቦና ዝግጅት አንጻር አበረታች መሆኑን አስረድተዋል።

በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ፕሬዚደንቱ አስረድተዋል

በእለቱ ክቡር ዶ/ር መኩርያ ሃይሌ የኢፌዲሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የእለቱ የክብር እንግዳ፣ ክቡራን የቦርድ አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የእለቱ የምረቃ በዓል በደመቀ ሁናቴ ተከናውኗል፡
ዘገባው የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ነው፡፡