በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፤ የመጨረሻ ፈጠራ ወይስ የፈጠራ መጨረሻ?” በሚል ወቅታዊና አነቃቂ ርዕስ በታዋቂው የቴክኖሎጂ ባለሙያና የሚዲያ ሰው አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ የቀረበ የሕዝብ ንግግር (Public Lecture) ተካሄደ።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በትምህርታዊ ዕውቀት ብቻ ሳይወሰኑ፣ በአስተሳሰብ፣ በፈጠራ ችሎታና በማኅበራዊ ክህሎቶች የዳበሩ፣ የተሟላ ስብዕና ያላቸው ዜጎች ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል በየሳምንቱ ረቡዕ ከሰዓትን ከመደበኛ የክፍል ትምህርት ነፃ በማድረግ ለተለያዩ የዕውቀት ማጋራት፣ የፈጠራና የስብዕና ማጎልበቻ መርሐ ግብሮች እያዋለ ይገኛል። ይህ የሕዝብ ንግግርም የዚሁ ተከታታይ ጥረት አካል ነው። በዝግጅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የተጋበዙ እንግዶችና ከአአሳቴዩ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት የተመረጡ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ ተሳታፊዎችን እንኳን ደኅና መጣችሁ በማለት፣ አቶ ሰለሞን ካሳ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያካበቱትን ሰፊ ልምድና ዕውቀት ለትውልዱ ተደራሽ ለማድረግ እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
አቶ ሰለሞን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በቴክቶክ (TechTalk) ፕሮግራማቸው ለ14 ዓመታት የቴክኖሎጂ ዕውቀትን ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ዕውቀታቸውን በመጽሐፍ መልክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። መጽሐፋቸውን ለማስመረቅና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሕዝብ ንግግር ለማቅረብ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመምጣታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።
እንደ አቶ ሰለሞን ያሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የሚያደርጉት የዕውቀት ማጋራት ብዙ ወጣቶችን ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለመሳብና የፈጠራ ፍላጎታቸውን ለማነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ተወዳዳሪና መሪ እንድትሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አመራር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መቋቋምን ጨምሮ፣ በማንሳት ተማሪዎች እነዚህን ዕድሎች ተጠቅመው በፈጠራና በምርምር ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ በበኩላቸው፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ወቅታዊ የዕድገት ደረጃ፣ በሰው ልጆች ሕይወትና በዓለም አቀፍ ልማት ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ እንዲሁም ወደፊት ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ በስፋት አብራርተዋል።
በተለይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለግለሰቦች፣ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ አህጉር የሚያስገኛቸውን መልካም አጋጣሚዎችና ሊያስከትላቸው የሚችሉ ስጋቶች በመዳሰስ፣ ስጋቶቹን በመቀነስና ዕድሎቹን በአግባቡ በመጠቀም ለወደፊቱ የተሻለ ዝግጅት ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶች አብራርተዋል።
በተጨማሪም፣ ከመቶ ዓመታት በኋላ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በሰው ልጆች ሕይወት፣ በሥራ ዓለምና በፈጠራ ሂደት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አዎንታዊና አሉታዊ ለውጥ በግምታዊ ሁኔታዎች በማስደገፍ አቅርበዋል። ይህም ተሳታፊዎች ስለ ቴክኖሎጂው የወደፊት አቅጣጫና የሰው ልጅ ሚና በጥልቀት እንዲያስቡ ዕድል ፈጥሯል።
በመጨረሻም በተማሪዎችና በተሳታፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በንግድ ባንክ ስፖንሰርነት ለ50 የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የመጽሐፍ ስጦታ ተበርክቷል።
የሕዝብ ንግግሩ ተማሪዎች ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲነሳሱና ለወደፊቱ የሚጠብቃቸውን ዕድልና ተግዳሮት በተሻለ መንገድ እንዲረዱ ያስቻለ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
© 2025 AASTU | Addis Ababa Science and Technology University
WordPress Theme by WPZOOM
ISO 9001:2015 certified organization by ECAE CD