Official University Website
በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 11ኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ (STEM) የፈጠራ ሥራዎች ውድድርና አውደ ርዕይ የአ.አ.ሳ.ቴ.ዩ የSTEM ማዕከል አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ተጠናቋል።በውድድሩ ላይ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የSTEM ማዕከልን ወክለው የቀረቡ አራት ተማሪዎች ባቀረቧቸው ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ከፍተኛ ብቃት አሳይተዋል። በዚህም መሠረት፡ መክሊት ሲሳይ የኤሌክትሮኒክስ ሰሌዳ (Printed circuit board) በመስራት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ ስትሆን የማርያም ሲሳይ በአጭር ጊዜ የአዕምሮ ህመምን በመመርመር የሚሳይ (Neural Triage) በመስራት በጤና ቴክኖሎጂ ዘርፍ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ሽልማትና የምስክር ወረቀት አግኝታለች።ከዚህ በዘለለ የአ.አ.ሳ.ቴ.ዩ የSTEM ማዕከል በውድድሩ ከተሳተፉ ሀገር አቀፍ የSTEM ማዕከላት መካከል በአጠቃላይ ውጤት 1ኛ ደረጃ በመውጣት የላቀ እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶለታል።የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብርሃም ደበበ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ አአሳቴዩ እንደ ሀገሪቱ ግንባር ቀደም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋምነቱ ለፈጠራ፣ ለምርምር እና ለወጣቶች ክህሎት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው የSTEM ማዕከሉን በማጠናከር በዙሪያው የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በመደገፍ ረገድ እያከናወነ ያለው ሥራ ዛሬ ለተገኘው አኩሪ ውጤት መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። ተማሪዎች ያቀረቧቸው የፈጠራ ሥራዎች የሳይንሳዊ ጉዟቸው መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ እንዳልሆነ የጠቆሙት ዶ/ር አብርሃም፣ ወጣት ተመራማሪዎች ከዚህም በላይ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሀሳቦችን በማመንጨት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።በመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ በበኩላቸው የፈጠራ ሥራዎች የንድፈ ሀሳብ ዕውቀትን በተግባር ላይ በማዋል ማኅበረሰባዊ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል። ተማሪዎች ተገቢው ድጋፍ ከተደረገላቸው ሳይንሳዊ ዕውቀታቸውን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር የሥራ ፈጣሪነት ክህሎታቸውን ማዳበር እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የስቴም ማዕከላት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያስተሳስሩ ወሳኝ ድልድዮች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ፕሮጀክቶች በግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚፈቱ አበረታች ተግባራዊ መፍትሄዎች የታዩባቸው መሆናቸውንም ጠቁመዋል።በውድድሩ ማጠቃለያ ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣ አሰልጣኝ መምህራን እንዲሁም አሸናፊ ለሆኑ የSTEM ማዕከላት ሽልማትና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል።የአ.አ.ሳ.ቴ.ዩን የሳይንስ፤ቴክኖሎጂ፤ ምህንድስና እና ሂሳብ ማዕከል በመወከል ለተወዳዳራችሁ ተማሪዎች ፤ አሸናፊዎች እና አሰልጣኝ እንኳን ደስ አላችሁ !